በ2013 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሄደ

ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ትኩረት መስጠቱ የግንባታውን ሂደት የበለጠ ለማቀላጠፍ አስተዋፅኦ ማድረጉ ተጠቆመ፡፡ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት 04 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2013 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም እና በ2014 ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስሊያጅ አቶ ቴዎድሮስ በላይ በውይይት መድረኩ ላይ ባቀረቡት የ2013 በጀት ዓመት ሪፖርት እንደጠቆሙት የከተማ አስተዳደሩ ለቤቶች ግንባታ የሰጠው ልዩ ትኩረት በተለያዩ ሰሳይቶች እየተካሄደ ያለውን ግንባታ ይበልጥ ለማቀላጠፍ እና በተሻለ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ካለው ክትትል በተጨማሪ የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትም ለቤቶች ግንባታ ትኩረት መስጠታቸው እንዲሁም ሥራ ተቋራጮች የግንባታ ግብዓቶችን እያቀረቡ የሚሠሩበትን አሠራር ለመዘርጋት ውለታ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱ አበረታች እንደነበረ ያመለከቱት ዋና ሥራ አስኪያጁ የሲሚንቶ እጥረት፤ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የገበያ አለመረጋጋት እና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አጋጥመው እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ባለፈው የበጀት ዓመት የግንባታ አፈፃፀማቸው ከ86 በመቶ በላይ የደረሱ ብሎኮች መኖራቸውን ጠቁመው በዘንድሮው የ2014 በጀት ዓመትም በነባር ግንባታ ላይ የሚገኙ 11,968 ህንፃዎችን እስከ መስከረም 30 እንዲሁም የተቀሩትን ደግሞ እስከ ታህሣሥ 30/2014 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም በ233 ነባርና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች አማካኝነት ለ3500 ዜጎች የሥራ ዕድል እና የ25 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደታቀደ አመልክተው ለ2014 በጀት ዓመት በዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን በሕዝብ ተሳትፎ በማሳካት እየተካሄደ ያለውን የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለማጠናከር በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በተለይ በየጊዜው እየናረ ከሚሄደው የግንባታ ግብዓት በተጨማሪ የሲሚንቶ እጥረት እንዳያጋጥም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉና ሌሎችም የግንባታውን ሂደት ይበልጥ ለማቀላጠፍ ያግዛል ያሏቸውን አስተያየቶችና ጥያቄዎች ሰንዝረው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለቀረቡት አስተያየቶችና ጥያቆዎች የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ከቤቱ የተሰነዘሩትን ገንቢ አስተያየቶች በግብዓትነት በመውሰድ ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመው በተለይ ከግንባታ ግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ለተሰነዘሩት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ባለሙያዎች እንዲሁም ከሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች የተውጣጣ ኮሚቴ አስፈላጊውን ጥናት አድርጎ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የተውጣጡ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ የተሰማሩ ሥራ ተቋራጮችና አማካዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡