በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተካሄደ

ቀን፡- ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጎን ለጎን ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ በሚደረገው እንቅስቃሴም በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና በተጠሪ ተቋማቱ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በይፋ ተጀምሯል፡፡

ከ2013 የክረምት የበጎ አድራጎት ተግባራት አንዱ የሆነው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በሚገኘው ቦሌ ቡልቡላ ሳይት እና አካባቢው በይፋ በተጀመረበት ወቅት የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መስከረም ዘውዴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ በተለይ ችግኞችን በመትከልና እንዲፀድቁም ትኩረት ሰጥቶ በመንከባከብ ከተማችንን አረንጓዴ ለማልበስ በሚደረገው ጥረት በንቃት መሳተፍና አሻራችንን ማኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ተክሎች የከተማችን ሳንባዎች ናቸው ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ የመኖሪያ ቤት መገንባት ብቻ በቂ ባለመሆኑ ኢትዮጵን እና ከተማችንን አረንጓዴ በማልበስ ለቀጣዩ ትውልድ ለምለም ሀገር በማስረከብ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በዕለቱ የተተከሉትን ሦስት ሺህ ችግኞችና አጠቃላይ ሥነ ስርዓቱን ሙሉ ወጪ የሸፈነው የጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አልማው ጋሪ በበኩላቸው ከቤቶች ግንባታ በተጨማሪ በአረንጓዴ የልማት መርሀ ግብር መሳተፍ የዜግነት ግዴታ መሆኑን አመልክተው ድርጅታቸው በቀጣይ በሚካሄዱ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ መሳተፉን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በክረምት የበጎ አድራጎት መርሀ ግብር ሰባ አምስት ሺህ ችግኞችን በ18ቱ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አማካኝነት በተለያዩ ሳይቶች ከመትከል በተጨማሪ ለሦስት ሺህ አረጋውያን የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ለማካሄድና ለአንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እንደታቀደ ታውቋል፡፡