ቤታቸው ለታደሰላቸው ነዋሪ የቁልፍ ርክክብ ተካሄደ::

ቀን፡- ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም

በክረምት የበጎ አድራጎት ተግባራ እየተካሄደ ያለው የአቅመ ደካማ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት የማደስ ተግባር ዘላቂነት ባለው መልኩ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በፕሮጀክት 4 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቤታቸው ለታደሰላቸው ነዋሪ የቁልፍ ማስረከብ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተካሄደው የቁልፍ ማስረከብ ሥነ ስርዓት ላይ የቤቶች ልማት ኮርፐፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ባደረጉት ንግግር ኮርፖሬሽኑ የችግረኛ ነዋሪዎችን ያረጁና የፈራረሱ የመኖሪያ ቤቶች ባለፉት ዓመታት የክረምት ወራትም በተደጋጋሚ ሲያድስ መቆየቱን አስታውሰው ይህን መሳሉ በጎ ተግባር አድማሱን አስፍቶ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የቤቶች ልማት ኮረትፖሬሽን በዘንድሮው የክረምት የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር መሠረት ከ45 በላይ የሚሆኑ የችግረኛ ነዋሪዎችን ቤቶች በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በማደስ ላይ እንደሚገኝ አመልክተው ኮንትራክተሮች፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለቤቶቹ እድሳት ያደረጉት ድጋፍ ለሌሎችም መልካም አርአያነት ያለው ነው ብለዋል፡፡
በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት 4 ዋና ሥ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ በላይ በበኩላቸው ቤታቸው ታድሶላቸው ቁልፍ ከተረከቡት አንዷ የሆኑትን የወይዘሮ አረጋሽ ታደሠን ቤት ለማደስ ኮንትራክተሮች ካደረጉት የአራት መቶ ሺህ ብር ወጪ በተጨማሪ የአልባሳት፣ የምግብ እህልና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ወይዘሮ አረጋሽ ታደሠም ቀደም ሲሎ ይኖሩበት የነበረው ቤት በክረምት ጎርፍ እየገባ ያስቸግራቸው እንደነበርና ድንገት ይፈርስብኛል ብለው በስጋት ይኖሩ እንደነበር ገልፀው አሁን ታድሶላቸው የገቡበት ቤት ለኑሮ ምቹ በመሆኑ ለበርካታ ዓመታት የኖሩበት ችግር ስለተቃለለላቸው መደሰታቸውን አመልክተዋል፡፡
ለታደሱትና እየታደሱ ለሚገኙት የአቅመ ደካማ አረጋውያን ቤቶች አስፈላጊው ወጪ የተሸፈነው በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ስር በሚገኙት የተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውስጥ በግንባታ ላይ የተሰማሩ ሥራ ተቋራጮች፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች መሆኑንም በወቅቱ ከተሰጠው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሥነ ስር ኣቱ ላይ ቤቶች ልማት ኮርፐፖሬሽን እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሥራ ተቋራጮች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡