ግንባታቸው በመፋጠን ላይ በሚገኙት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉብኝት ተካሄደ
ሰኔ2013 ዓ.ም
ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጎን ለጎን ለመሠረተ ልማት ግንባታም የተሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን በተቀናጀ አሠራር ለማጠናቀቅ የተቋቋሙት የአቢይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሥራ ኃላፊዎችና አባላት በተለያዩ ሳይቶች ግንባታቸው በመፋጠን ላይ የሚገኙትን ቤቶች ጎብኝተዋል፡፡
ግንባታውን በተቀናጀ አሠራር ለማጠናቀቅ ከተቋቋሙት አቢይና የቴክኒክ ኮሚቴዎች እንዲሁም ከቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና ከተጠሪ ተቋማት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና አባላት በቦሌ በሻሌ፣ በቦሌ አራብሳ ሳይቶች እና በፕሮጀክት 4 ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በተካሄደው የሥራ ጉብኝት ላይ የአቢይ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ እንደገለፁት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን አጠናቆ ለህብረተሰቡ ለማስተላለፍ በሚደረገው ርብርብ ለመሠረተ ልማት ግንባታም የተሰጠው ልዩ ትኩረት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በግንባታው ላይ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በየጊዜው ከሚያነሷቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል አንዱ ለሆነው የሲሚንቶ እጥረት የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ይድነቃቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች አጠናቆ ለማስተላለፍና የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መስከረም ዘውዴ፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት እና በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ለሲሚንቶ እጥረት የተሰጠው ልዩ ትኩረት ተገቢ መሆኑን አመልክተው የሲሚንቶ አቅርቦት የማያስፈልጋቸው ሌሎች ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ለግንባታው ይበልጥ መፋጠን መንገድ መብራትና ውሃን የመሰሉ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶችን በሚፈለገው ደረጃ ማግኘት የጎላ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ሌዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ተወካዮችም በተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ በአባላነት እንዲታቀፉ መደረጉ የተቀናጀ አሠራር የሚያስችልና ለተሻለ ስኬት የሚያበቃ በመሆኑ የኮሚቴው አባላት በንቃት እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የአቢይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አመራር አባላት እንዲሁም የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡