የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞች የዘንድሮውን የሠንደቅ አላማ ቀን አከበሩ፡፡
“በአዲስ ምዕራፍ፣ በተሟላ ሉአላዊነት፣ ለሠንደቅ አላማችን ከፍታ!” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ በተከበረው የሠንደቅ አላማ ቀን ላይ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ያስሚን ወሀቢ ባደረጉት ንግግር ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በድል ተጠናቆ ሀገሪቱ በአዲስ ምዕራፍ ለተሻለ ስኬት ቆርጣ በተነሳችበት ማግስት መካሄዱ የዘንድሮውን የሠንደቅ አላማ ቀን የተለየ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡
አሸናፊው ፓርቲ አዲስ በተቋቋመው መንግስት ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በካቢኔ አባልነት እንዲካተቱ ማድረጉ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከናወነ ተግባር እንደሆነ ያስታወሱት የቢሮ ኃላፊዋ በቀጣይም ኢትዮጵያን ለማበልፀግ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ወገን የዜግነት ግድታውን ለመወጣት ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ በሠንደቅ አላማ አከባበር ሥነ ስርዓቱ ላይ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡