የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በአስኮ ሳይት 40-60 2ኛ ዙር ቤት እድለኞች የቁልፍ ርክክብ አደረገ
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በአስኮ ሳይት 40/60 2ኛ ዙር ቤት እድለኞች የቁልፍ ርክክብ አደረገ
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ሓላፊ ዶ/ር መስከረም ዘውዴ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በ10/20/13ዓም የመስክ ጉብኝት ከማድረጋቸው በተጨማሪ በ2ኛ ዙር የቤት እጣ ደርሷቸው በተለያዩ ምክንያቶች ቁልፍ ሳይረከቡ ለቀሩ ለሁለት ብሎክ ነዋሪዎች የቁልፍ ርክክብ አድርገዋል፡፡
ደ/ር መስከረም ዘውዴ በስነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት በቅርቡ የከተማው አስተዳደር ባወረደው እቅጣጫ መሰረት እጣ ወጥቶላቸው እስካሁን ቁልፍ ተረክበው ወደ ቤታቸው እንዳይገቡ ያደረጓቸውን ቀሪ ስራዎች በማጠናቀቅ ቁልፍ እንዲረከቡ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው ከዚህ በኋላ በ20/80 እና በ40/60 ቁልፍ ያልተረከቡትን በመለየት ተራ በተራ በሂደት እንደሚያሥረክቡ ገልጸዋል፡፡
በአስኮ ሳይት የመንገድ የፍሳሽ እና የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ስራዎች በጥሩ ደረጃ ላይ እነደሆነ የገለጹት ቢሮ ሃላፊዋ ቀሪስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ርክክብ ሊደረግባቸው እንደሚገባም አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶሽመልስ ታምራት በበኩላቸው የአስኮ ሳይት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አፈጻጸም በጥሩ ጎኑ እንደሚያዩት ገልጸው ውሀ እና ኤሌክትሪክ በፍጥነት ከመኖሪያ ቤት ጋር የማገናኘት ስራዎች እንዲፋጠኑ አሳስበዋል፡፡
የፕሮጀክት 1 ቅርኝጫፍ ጽ/ቤት ዋና ስራስኪያጅ አቶስዩም ገብሬ አሁን ላይ ከመሰረተ ልማት አንጻር የነበሩ ግብኣት ችግሮች እየተቀረፉ እና የመንገድ ስራዎች እየተጠናቀቁ በመሆናቸው የመብራት እና የውሃ ቆጣሪ በበቂ ሁኔታ መረከባቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ሳምንት የቤት ለቤት ዝርጋታ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በአስኮ ሳይት እስካሁን ለ8 ብሎክ ነዋሪዎች ቁልፍ የማስረከብ ስራ እንደተከናወነ ጠቁመው ለሁለት ብሎክ ነዋሪዎች ቁልፍ ርክክብ መፈጸሙን አስታውቀዋል፡፡