በክረምት የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር የተከናወኑትን ተግባራት በበጋ ወራትም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በቦሌ ሃያት ክላስተር ስር የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና ቅርንጫፍ 12 ጽ/ቤት ያስገነቧቸው የችገረኛ ነዋሪዎች ቤቶች ተጠናቀው የቁልፍ ርክክብ ተካሂዷል፡፡

በልደታ እና በየካ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በቦሌ ሃያት ክላስተር አማካኝነት በተካሄደው የቁልፍ ርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ባደረጉት ንግግር በክረምት የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች ማዕድ ከማጋራት፣ የምግብና የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ያረጁና የፈራረሱ ቤቶቻቸውን ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ አድርጎ እንደገና በመገንባት የተከናወነው ተግባር አበረታች መሆኑን አስታውሰው በመጪዎቹ የበጋ ወራትም ይህንኑ መልካም ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል እንደታቀደ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው የክረምት የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር ከ10 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ከ45 በላይ የሚሆኑ የችግረኛ ነዋሪዎችን ያረጁ እና የፈራረሱ ቤቶች በማደስ ለኑሮ ምቹ ማድረግ እንደተቻለ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ኮንትራክተሮች፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለቤቶቹ እድሳት ያደረጉት ድጋፍ ለሌሎችም መልካም አርአያነት ያለው ነው ብለዋል፡፡ 

በቦሌ ሃያት ክላስተር ስር የሚገኙት ቅርንጫፍ 2፣ 3 እና 4 እንዲሁም 5 እና 17 ዋና ሥራ አስኪያጆችና የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በዕለቱ የቁልፍ ርክክብ የተካሄደባቸው ሰባቱ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ፈርሰው ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንደገና የተገነቡ መሆኑን ገልፀው ለዚህም ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ  የቦሌ ሃያት ክላስተር ምንም የመተዳደሪያ ገቢ ለሌላቸው ነዋሪ የገዛላቸውን የቺፕስ መሥሪያ ማሽን በስጦታ አበርክቷል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የቅርንጫፍ 12 ጽ/ቤት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የሦስት ችግረኛ ነዋሪዎችን ቤቶች ሙሉ በሙሉ አፍርሶ እንደገና በመገንባት ቁልፎቻቸውን ለነዋሪዎቹ አስረክቧል፡፡

በቁልፍ ርክክቡ ሥነ ስርዓት ላይ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው መኮንን ባደረጉት ንግግር በክረምት የበጎ አደስራጎት ተግባር የተከናወነው የቤቶች ዕድሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የችግረኛ ነዋሪዎችን የፈራረሱ ቤቶች በማደስ ያሳዩትን አርአያነት በመከተል የተከናወነ መሆኑን አመልክተው በዕለቱ የቁልፍ ርክክብ ለተካሄደባቸው ቤቶች ከአንድ ሚሊየን አንድ መቶ ሃምሣ ሺህ ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ጠቁመዋል፡፡    

ከተገነቡት ቤቶች መካከል ባለ አንድ ወለል ቤት የሚገኝበት ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከቤቶቹ ግንባታ በተጨማሪ ለአንዲት ችግረኛ አረጋዊ እናት ያሉበትን የከፋ ችግርኛ በመገንዘብ የመቀመጫ ሶፋ እና የመኝታ አልጋ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡    

በክረምት የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር በልደታ፣ የካ እና አራዳ ክፍለ ከተሞች  በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የችግረኛ ነዋሪዎችን ቤቶች አፍርሶ ለኑሮ ምቹ አድርጎ እንደገና ለመገንባት በተደረገው እንቅስቃሴ ሥራ ተቋራጮች፣ ማህበራትና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ገንዘባቸውን ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ያበረከቱት ድጋፍ ለቤቶቹ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የሥራ ኃላፊዎቹ አመልክተው በቀጣይም በክረምት የተጀመረውን የበጎ አድራጎት ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በቦሌ ሃያት ክላስተርና በፕሮጀክት 12 በተካሄደው የቁልፍ ርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ በክረምት የበጎ አድራጎት መርሃ ግብር በንቃት የተሳተፉ ሥራ ተቋራጮች፣ ማህበራትና ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት የተረከቡ ሲሆን በተለይ በቦሌ ሃያት ክላስተር ባበረከቱት አስተዋፅኦ ልቀው የተገኙ ሥራ ተቋራጮችና ማህበራት የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡