የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የምእራብ ክላስተር ቅርንጫፎች 4000 ችግኞችን ተክለዋል

ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ የሚለውን ጥሪ መነሻ በማድረግ ከሚደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በተጨማሪ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች በማድስ ለኑሮ ምቹ ማድረግ እንዲሚገባ ተገለፀ፡፡
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ስር የሚገኘው የምዕራብ ክላስተር በክረምት የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር እቅድ መሠረት የ6ቱ ክላስተር ጥምሮች አራት ሺህ ችግኞችን ከስድስቱ ቅርንጫፍ ከተውጣጡ 600 በላይ ሠራተኞችና 120 ባለድርሻ አካላት በማስተፍ በቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 የችግኝ ተከላ አከናውነዋል፡፡ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ቶማስ ደበሌ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በሃገራችን ያሉትን በረሃ ስፍራዎች ከመባባስ ለመታደግ እንደሚረዳ ገልፀው አሁን የታየው የአየር ለውጥ የተገኘው ቀደም ሲል በተደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የመጣ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቤቶች ልማት ኮርፖሬሸን የኘሮጀክት 6 ዋና ስራ አስኪያጅና የምዕራብ ክላስተር አስተባባሪ ኢ/ር ሚሊዩን የኋላሸት እንደገለፁት ደግሞ ከችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ባሻገር በክላስተሩ አስተባባሪነት ከ20 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤት ለማደስ ዝግጅት መደረጉንና ከ17 በላይ ቤቶች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ላይ እድሳቱ እንደሚደረግ በዕድሳቱም ኮንትራክተሮችና ማህበራት እንደሚሸፍኑም ነው የተናገሩት ፡፡ ሌሎች አካላት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውንም አሳውቀዋል፡፡
የክላስተር አስተባባሪው ኢ/ር ሚሊዩን የኋላሸት ከ6ቱም ቅርጫፍ ደም ለመለገስ ፍቃደኛ የሆኑ ከ100 በላይ ሠራተኞች የደም ልገሳ ለማድረግ መዘጋጅታቸውንና ከዛም ጎን ለጎን አንድ ሠው ለአንድ ቤተሠብ የማዕድ ማጋራት ኘሮግራም በቀጣይ እንደሚደረግ ገልፀው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚገባ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡