20/03/2014

ህብረተሰቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት የተቀናጀ አሠራር መዘርጋትና በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የመንግስትና የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክቶሬቶች የ2014 በጀት ዓመት የአራት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እንዲሁም በቢሮው ስልጣንና ተግባራት ላይ ያተኮረ ውይይት ከክፍለ ከተማ እና ወረዳ ከተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተካሂዷል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ያስሚን መሃብረቢ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ህብረተሰቡን በቅርበት የሚያገለግሉ በመሆናቸው ህብረተሰቡ በየደረጃቀው ለሚያነሳቸው የመልካም አሰተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት ይበልጥ ተቀናጅተው በጋራ መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተው ከቤት ልማት ፕሮግራሙ ጋር በተያያዘ ቢሮው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ በቀረበው የመንግስት እና የጋራ መኖሪያ ቤት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የ2014 በጀት ዓመት የአራት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የቁልፍ እና የአበይት ተግባራት አፈፃፀም እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ መፍትሔዎች የቀረበ ሲሆን በተለይም የ48,958 የመንግስት መኖሪያ በቶች እና የ9,535 ንግድ ቤቶችን ውል በማደስ እንዲሁም ለ5,449 የመንግስት ቤቶች ፋይል ካርታ በመሥራት ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደተቻለ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

ባለጉዳዮች የክፍለ ከተማ መዋቅር ሳያናግሩ ወደ ማዕከል በመምጣት ለአላስፈላጊ እንግልት እንደሚጋለጡ ያመለከተው ሪፖርቱ በቀበሌ ቤቶች አስተዳደር እና በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ የሚስተዋሉ  የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሠጣጥ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መፍታት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

በሌላም በኩል በአዋጅ ቁጥር 74/2014 መነሻነት ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የተሰጡት ስልጣንና ተግባራት በመድረኩ ላይ የቀረበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ቢሮው የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን በበላይነት ከመምራት በተጨማሪ በቤት ልማት ፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡና በባንክ የሚቆጥቡ ነዋሪዎችን የቁጠባ ገንዘብ መጠቀም የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገኙበት በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ተሳታፊዎች በተለይ የቤት ኪራይ ውል ሳይዋዋሉ ለረጅም ዓመታት የኖሩ ግለሰቦች መኖራቸው፣ የካርታ እና የይዞታ ጉዳዮች አስቸኳይ እልባት እንዲሰጣቸው የሚሉ እና ሌሎችም አስተያየቶችና ጥያቄዎች ሰንዝረው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ለበርካታ ዓመታት ኖረው ህጋዊ ውል የሌላቸውን ነዋሪዎችና ሌሎችንም ጉዳዮች  የሚመለከት ሙሉ መረጃ በመያዝ ለቢሮው ማሳወቅ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን የመንግስት ቤቶችን ከህግ አግባብ ውጪ ለግለሰቦች መስጠት የመልካም አስተዳደር ችግር ከመሆኑ በተጨማሪ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ቨበመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግበትም ተገልጿል፡፡        

 በውይይት መድረኩ ላይ ከአሥራ አንዱም ክፍለ ከተሞችና በስራቸው ከሚገኙት ወረዳዎች እንዲሁም ከቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና ከቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡