ህዳር 02/2014 ዓ.ም
የኢትዮዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሁለገብ ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ግዴታን መወጣት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል፡፡
“ደማችን ለመከላከያ ሠራዊታችን!!” በሚል መርህ በመሥሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ በተካሄደው የደም ልገሳ ሥነ ስርዓት ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ያስሚን ወሀብረቢ ባደረጉት ንግግር የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገር ህልውና እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት መላው ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች የበኩላቸውን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠልና” ከሠራዊቱ ጎን በቁርጠኝነት መሰለፍ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
የቢሮውና የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ደማቸውን ለሠራዊቱ በመለገስ አጋርነታቸውን በተግባር ማስመስከራቸው ሀገራቸው የምትጠይቀውን ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛ መሆናቸውን ያሳያል ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ በቀጣይም ሀብት በማሰባሰብና በሌሎችም ተግባራት ሀገርን ለማዳን እየተደረገ ያለውን ትግል ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ደም ከለገሱ ሠራተኞች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለዜጎች በሠላም መኖር መስዋዕትነት እየከፈለ በመሆኑ ደማቸውን ለሠራዊቱ በመለገስ አጋርነታቸውን ለመግለፅና ከጎኑ መሆናቸውን በተግባር ለማሳየት ደም መለገሳቸውን ገልፀዋል፡፡
በሥነ ስርዓቱ ላይ የቢሮው እና የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም የለገሱ ሲሆን በቀጣይም በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት ደም የመለገስ፣ ሀብት የማሰባሰብና ሌሎችም ተግባራት እንደሚከናወኑ ታውቋል፡፡