ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ከሀገር መከላከያ ጎን በመሰለፍ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገለፁ፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ ህወሀት በፈፀመዉ ጥቃት ለተሰው ሰማዕታት የህሊና ፀሎት አድርገዋል፡፡
የቢሮውና የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች “አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ፡፡” በሚል መሪ ቃል ከአንድ ዓመት በፊት ህወሀት በፈፀመው ጥቃት በግፍ ለተሰዉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሻማ በማብራትና የህሊና ፀሎት በማድረግ ለሠራዊቱ ያላቸውን አጋርነት የገለፁ ሲሆን ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል፡፡
የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ሽብርተኛው የህወሀት ቡድን ሀገርን ለማፍረስ ከሚያካሂደው ጦርነት በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችና መገናኛ ብዙሀን ሀሰተኛ ወሬ በመንዛት ህዝብን ማሸበር ዋነኛ ተግባሩ መሆኑን ጠቁመው ቡድኑ ከሚያሰራጨው የተዛባ ወሬ መጠንቀቅና የሀገርን ሠላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ በጋራ መረባረብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተሪኳ ተሸንፋ አታውቅም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ህወሀት በሀገር ህልውና ላይ የከፈተውን አደጋ ለመቋቋም እየተደረገ ባለው ትግልም እስከመጨረሻው የድል ብስራት ድረስ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
መላው ሠራተኛም በተሰማራበት የሥራ መስክ ከምንጊዜውም በበለጠ ጠንክሮ መሥራትና የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ሠንደቅ ዓላማ የማውጣት ሥነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን የቢሮውና የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡