የመንግስት ቤቶች ማስተዳደር
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ንብረት ለማድረግ በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 47/1967 መሰረት የተወረሱ የቀበሌ ቤቶች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ መንገዶች ተገንብተው መንግስት የሚያስተዳድራቸው የመንግስት መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ቤቶች ለመኖሪያነትና ለንግድ አገልግሎት ጠቀሜታ እየዋሉ ቢገኙም ቤቶቹ እድሳት ሳይደረግላቸው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ከመሆናቸውም በላይ በጣም ያረጁና የከተማውን ውበት የጠበቁ ባለመሆናቸው በአሁኑ ወቅት ያሉበት አካባቢ ደረጃ በደረጃ ለከተማ መልሶ ማልማት ግንባታ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ የከተማው አስተዳደር በራሱ በጀት ያስገነባቸው የቁጠባ ቤቶች ከፊሉ በረጅም ጊዜ ብድር ክፍያ ለነዋሪዎች የተላለፉ ሲሆን፤ የተቀሩት ደግሞ በአስተዳደሩ ይዞታ በኪራይ መልክ ለመኖሪያ አገልግሎት እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የመንግስት ቤቶቹ ለረጅም ዓመታት ትኩረት ያልተሰጣቸው በመሆናቸዉ መረጃቸው በአግባቡ ያልተደራጀ ከመሆኑም ባሻገር የፈረሱ እና አገልግሎት እየሰጡ ያሉ መኖሪያና ንግድ ቤቶች ያሉበት ሁኔታ በአግባቡ ባለመለየቱ ምክንያት ለቁጥጥርና ክትትል አመቺ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ ቆይቷል፡፡
ከዚህ በመነሳት የከተማ አስተዳደሩ በመንግስት ቤቶች አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በ1996 እና በ2004ዓ.ም የመንግስት ቤቶች አስተዳደር ደንብ ከማውጣቱ ባሻገር ቤቶችን በማዕከላዊነት የሚከታተልና የሚያስተዳድር ተቋም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የመንግስት ቤቶች አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 4/2009 አውጥቶ ተግባር ላይ የዋለ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ስልጣንና ተግባር ሙሉ በሙሉ ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በመተላለፉ፣ የመንግስት ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የተዘጋጀና እየተዘጋጀ ያለ በመሆኑና ይህ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አያያዝና የይዞታ አጠቃቀም የሚገልፅ ጉዳይ በመመሪያው ያልተካተቱ እንዲሁም ሊስተካከሉ የሚገባ ጉዳዮች በመኖራቸው የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚና ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት እንደገና በወጣው ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 64/2011 አውጥቷል፡፡
ዓላማ
የመንግስት ቤቶች አስተዳደር የሚከተሉት አላማዎች አሉት
-
- በከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪዎች የሚደረገውን የመኖሪያና መስሪያ ቦታ አቅርቦት ጥረት በቤት ኪራይ አማራጭ የሚደረገውን አበርክቶ ስርዓት አሻሽሎ ማስቀጠል፤
- በቢሮዉ የቤት መረጃ አያያዝ፣ የማከራየት ሂደት፣ የቤት አሰጣጥ፣ የቤት ቅያሬ፣ የቤት የኪራይ አከፋፈል፣ የቤት ጥገና እና በሚወጡት አሰራሮች ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፤
- የሚለቀቁ ክፍት ቤቶችን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ማከራየት
- በቤቶች ላይ የሚፈጸሙትን ህገወጥ ተግባራት መከላከልና በህገወጦች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ
- በተለያዩ ምክንያቶች መንግስት ሊያስተዳድራቸው ሲገባ በመንግስት እጅ ያልነበሩ ቤቶችን ወደ መንግስት አስተዳደር እንዲገቡ በማድረግ የቤት አስተዳደር ስርዓቱን ማዘመን፤
- ከአቅም በታች አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የመንግስት ቤቶችን ቦታ በዳግም ልማት ወይም ጥገና ተጨማሪ የቤት አቅርቦት እንዲሰፋ ማስቻል፡፡
ቤት እንዴት ይተዳደራል?
የ አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በአዋጅ 47/1967 የተወረሱ ቤቶችን፣ከአዋጁም በኋላ በከተማ አስተዳደሩ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የተገነቡ ቤቶችን ከተማ አስተዳደሩ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ያስተዳድራል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 47/1967 የተወረሱ ቤቶችን በተመለከተ
-
- ቢሮው በአዋጁ የተወረሱ ቤቶችን ቆጠራ በማካሄድ ያሉና የፈረሱ ቤቶችን እንዲሁም ለባለቤቶቹ የተመለሱትን በመለየት መረጃ በአግባቡ ያደራጃል፤
- የተለዩ ቤቶችን የተከራይ መረጃን፣ የቤቱን ዓይነትና ደረጃ እንዲሁም የግልና የጋራ መገልገያ ቤቶችን እና ክፍት ቤቶችን በቋሚ መዝገብ ይመዘግባል፤ ያደራጃል፤ እንዲሁም የፈረሱ ቤቶችን መፍረሳቸውን በማረጋገጥ ከቋሚ መዝገብ እንዲሰረዝ ያደርጋል፤
- መረጃተው የተደራጁ ቤቶችን በአድራሻና በቤት ቁጥር ከለየ በኋላ በዘመናዊ መረጃ አደራጅቶ በሶፍትና በሀርድ ኮፒ እንዲሁም እንደሁኔታው የምስል መረጃ መያዝ ይይዛል
- የመንግስት ቤት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሚሰራላቸውን ቤቶች እና ይዞታዎችን መረጃ በማደራጀት ለሚመለከተው አካል መረጃውን በመላክ ካርታው ተሰርቶ ሲጠናቀቅ አስፈላጊውን ርክክብ ያደርጋል፤
- የመንግስት ቤቶችና ይዞታዎች ካርታ እንዲሰራላቸው በማድረግ መረጃው አደራጅቶ ያስቀምጣል፡፡
ከአዋጁ በኋላ በአስተዳደሩ የተገነቡ ቤቶችን በተመለከተ
-
- በከተማው አስተደዳር ውስጥ በተለያየ ጊዜ አስተዳደሩ የገነባቸውን ቤቶች ቆጠራ በማካሄድ ያሉና የፈረሱ ቤቶችን ይለያል፤
- የተለዩ ቤቶችን የተከራይ ማንነት፣ የቤቱን ዓይነትና ደረጃ እንዲሁም የግልና የጋራ መገልገያ ቤቶችን በቋሚ መዝገብ ይመዘግባል፤ ያደራጃል፤ በልማት ወይም በእርጅና የፈረሱ ቤቶችን መፍረሳቸውን እያረጋገጠ ከቋሚ መዝገብ እንዲሰረዝ ይደረጋል፤ የተሰረዙትን ቤቶች በቃለ ጉባኤ በመያዝ በወረዳው ካቢኔ ቤቶቹ በልማት ወይም በእርጅና የፈረሱ ስለመሆናቸው ተወስኖ መረጃውን ይይዛል ለበላይ አካላትም ሪፖርት ይደረጋል፤
- አስተዳደሩ ገንብቷቸው ነገር ግን ቢሮው የማያስተዳደራቸው ቤቶችን ባለቤትን ለመወሰን የሚያስችሉ የመንግስት ቤቶችን መረጃ አደራጅቶ ለከተማ አስተዳደሩ ለውሳኔ ያቀርባል፤
ከአዋጁ በኋላ በመንግስታዊ ድርጅት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ እና በግል ድርጅቶች የተገነቡ እና መንግስት የሚያስተዳድራቸው እና ሊያስተዳድራቸው ስለሚገባ ቤቶችን በተመለከተ
-
-
- ቢሮው በከተማው አስተዳደር ውስጥ በተለያዩ ጊዜ መንግስታዊ ባልሆኑ፣ የግል እና የመንግስት ድርጅቶች የተገነቡና መንግስት የሚያስተዳድራቸውና ሊያስተዳድራቸው የሚገባ ቤቶችን ቢያንስ በሁለት አመት አንድ ጊዜ ቆጠራ ያካሂዳል፤
- ቆጠራው ሲከናወን በቤቱ ውስጥ እየኖሩ ያሉት ነዋሪዎች ቤቱን በምን አግባብ እንዳገኙት፣ ቤቱን ከመያዛቸው በፊት ይኖሩበት የነበረበት ሁኔታ እና በአሁኑ ጊዜ ቤቱ በማን ባለቤትነት እንደተያዘና ባለቤትነቱም በግለሰብ ከሆነ የተላለፈበትን በዘመናዊ መረጃ አደራጅቶ በሶፍትና በሀርድ ኮፒ መያዝ አለበት፤
- ቤቶችን በቤት ዓይነትና ደረጃ እንዲሁም የግልና የጋራ መገልገያ ቤቶችን መረጃ መዝግቦ አደራጅቶ ይይዛል፤
- በተለያየ ጊዜ መንግስታዊ ያልሆኑ እና የግል እንዲሁም የመንግስት ድርጅቶች ቤቶቹን ገንብተው ነገር ግን ቢሮው የማያስተዳድራቸውን ቤቶች ባለቤትን ለመወሰን የሚያስችሉ የቤቶቹን መረጃ አደራጅቶ ለከተማው አስተዳደር ለውሳኔ ያቀርባል፤
- መንግስታዊ ባልሆኑ እና የግል እንዲሁም የመንግስት ድርጅቶች በወረዳው አስተዳደር ውስጥ ተገንብተው ርክክብ የተደረገባቸው እንዲሁም ለወረዳው አስተዳደር በስጦታ ወይም በማናቸውም ህጋዊ መንገድ የተላለፉለትን ቤቶች የወረዳው አስተዳደር ወዲያውኑ በክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት በኩል ለቢሮው ያሳውቃል፡፡
-
በመንግስት ቤቶች አስተዳደር ስር የሚሰጡ አገልግሎቶች
-
-
-
- የከተማ አስተዳደሩ ንብረት የሆኑ የመኖሪያ፣ ንግድና ሌሎች ቤቶችን ለማከራየትና ለማስተዳደር ለመምራት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍና ስልቶችን ያዘጋጃል፣ ይተገብራል፡፡
- የከተማ አስተዳደሩ ንብረት የሆኑ የመኖሪያ፣ ንግድና ሌሎች ቤቶችን በፍትሐዊነት ያስተዳድራል፤ቤቶችን በህግ መሠረት ያከራያል፤ የተለያዩ አማራጭ የኪራይ ተመን ያጠናልሰ ሲጸድቅ ይተገብራል፤ ወርሃዊ የቤት ኪራይ ይሰበስባል፤ መሰብሰቡን ይከታተላልሰ፡፡
- የመንግስት የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በህገ-ወጥ መንገድ ከያዙት አካላት ያስለቅቃል፡፡
- ቤቶቹ በልማት ምክንያት በሚፈርሱበት ወቅት አስፈላጊውን መረጃ ለሚመለከተው አካል ያስተላልፋል፤ በቤቱ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ምትክ ቤት የሚያገኙበትን አግባብ ያመቻቻል፡፡
- የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች ጥገናና እድሳት ያደርጋል፡፡
- በአነስተኛና መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ነዋሪዎች በተለይም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የልማት ተነሺዎች በቤት ልማት ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
- ከቤት ሽያጭ፣ ኪራይና የመሳሰሉት ተግባራት ላይ ጤናማ የገበያ ስርዓት እንዲኖር የሚያስችል ጥናቶችን ያጠናል፤ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
- የቤት ኪራይ ፍላጎት መለየት የሚያስችል ዝርዝር ጥናት ያከናውናል፤የኪራይ ቤት አቅርቦት ክፍተቶችን መድፈን የሚያስችል የመፍትሔ ኃሳቦችን ያመነጫል፤ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ያስወስናል፤ ይተገብራል፤ አፈጻጸሙንም ይከታተላል፡፡
- የመንግስት ቤቶች ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲወጣላቸው ክትትል ያደርጋል፣ለካርታ ስራ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን ለሚመለከተዉ አካል ይሰጣል፡፡
- የመንግስት ቤቶች ይዞታ መረጃ በየደረጃዉ በአግባቡ መያዙን ክትትል ያደርጋል፡፡
- የመንግስት ቤቶችን ይዞታ ያስተዳድራል፡፡
- የጋራ መኖሪያ ቤት ሆኖ ለመምህራን፤ለመንግስት ሰራተኛ፤ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የከተማ ነዋሪዎች በኪራይ የተሰጡትን ቤቶች በፍትሐዊነት ያስተዳድራል፤ቤቶችን በህግ መሠረት ያከራያል፤ የተለያዩ አማራጭ የኪራይ ተመን ያጠናል፤ሲጸድቅ ይተገብራል፤ወርሃዊ የቤት ኪራይ መሰብሰቡን ይከታተላል፡፡
- በተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች የተፈናቀሉ ማለትም ቤታቸዉ በጎርፍ፣በእሳት፣በመሬት መንቀጥቀጥና በሌሎች አደጋዎች ቤት አልባ የሆኑ የከተማ ነዋሪዎችን ጉዳዩ ከሚመለከተዉ አካል ላይ መረጃዉን በመቀበልና በማጣራት ምትክ መኖሪያ ቤት የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡
- በመንግስት ቤቶች ይዞታና ሌሎች አጎራባች መካከል የወሰን ይከበርልኝ ጥያቄ ሲኖር አስፈላጊዉን መረጃ አደራጅቶ ለሚመለከተዉ አካል ያቀርባል፡፡
- ቤቶቹ በልማት ምክንያት በሚፈርሱበት ወቅት አስፈላጊውን መረጃ ለሚመለከተው አካል ያስተላልፋል፡፡
- በቤቱ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ምትክ ቤት የሚያገኙበትን አግባብ ያመቻቻል፡፡
- ለመልሶ ማልማት የሚፈለጉ ቦታዎች(አካባቢዎች) መረጃ ከሚመለከተው አካል ይረከባል፡፡
-
-