ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አካሄደ
በ2014 በጀት ዓመት በእቅድ የተያዙ ተግባራትን በተሻለ ስኬት ለማጠናቀቅ በቤቶች ልማት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች እና የባለድርሻ አካላት በተጠያቂነት እና በኃላፊነት መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡
አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የ2013 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2014 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡
በ2014 በጀት ዓመት በእቅድ የያዛቸውን ተግባራት አስመልክቶ በግሎባል ሆቴል በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልሽስ ታምራት በበጀት ዓመቱ የተያዙትን የእቅድ ተግባራት ከግብ ለማድረስ እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች እና የስራ ኃላፊዎች በእውቀት በታማኝነት እና በቅንጅት በመስራት ኃገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት እና ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ በማስተላለፍ ሂደት ውስጥም የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በእውቀት የሚመራ፣ የሰለጠነ እና ዘመናዊ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት እና በዘርፉ ውስጥ ስር ሰዶ የተሰራፋውን ቢሮክራሲያዊ አሰራሮችን በመታገል በበጀት ዓመቱ የታቀዱትን የቤት ልማት ተግባራትበተሻለ አፈጻጸም ማጠናቀቅ እንደሚቻል ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከመንግስት እና ከህዝብ የተሰጠውን ተልእኮ በተሻለ ሁኔታ ለማጠናቀቅ 2013 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸምን እና የ2013-2017 የተዘጋጀውን የስትራቴጂክ እቅድ እንዲሁም የተቋሙ አመራር እና ሰራተኛው ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ፣ ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት እቅድ ማዘጋጀቱን የእቅድ እና በጀት ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ደንቦባ ገልጸዋል፡፡
አቶ አለማየሁ በሪፖርታቸው ላይ እንደገለጹት በ2014 በጀት ዓመት በ20/80 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በተመለከተ በነባር ግንባታ ላይ የሚገኙ 139,008 ቤቶችን ማጠናቀቅ እና በ2012 በጀት ዓመት የተጀመሩ 4,287 የቤቶች ግንባታን የተሻለ ደረጃ ማድረስ ሲሆን እንዲሁም በ2014 በጀት ዓመትበ20/80 49,967፣ በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም 34,866 ቤቶች እና ለኪራይ የሚገነቡ 9,330ቤቶች በድምሩ 94,163 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ለማስጀመር በእቅድ መያዙን ነው፡፡
በ2014 በጀት ዓመት እቅድ የተያዘው የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ለ3,484 ነባር እና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ለ36,462 ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር እና የ1,ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር እንደሚኖረው ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በመጨረሻም አቶ አለማየሁ በሪፖርታቸው ላይ 43,987 የ20/80 እናየ40/60 የጋራ መኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ በእጣ እና በጨረታ እንደሚተላለፍ ገልጸዋል፡፡