ኮርፖሬሽኑ በ13ኛ ዙር እጣ ከወጣላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አካሄደ

04/10/13

ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉ እና የመሰረተ ልማት አውታሮች ሳይሟላላቸው ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በ13 ኛ ዙር በእጣ የተላለፉ የኮዬ ፈጬ ሳይት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በአጭር ጊዜውስጥ ማጠናቀቅ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተቀዳሚ ተልዕኮ ሊሆን እንደሚገባው ተጠቆመ፡፡

በኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ከተላለፈላቸው የአዲስ አበባ ማህበረሰብ ጋር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ውይይት አካሂዷል፡፡ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ያስችል ዘንድ በማኅበረሰቡ ከተወከሉ ኮሚቴዎች ጋር ተዋህደው ሊሰሩ በሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታዎች ላይም መክረዋል፡፡

በኮዬ ፈጬ ሳይት ፕሮጀክት አስራ አንድ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አዳራሽ ከቤት እድለኞች ጋር በተካሄደ ውይይት የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በመቀዛቀዙ ምክንያት በተያዘላቸው እቅድ መሰረት የቤቶችን ግንባታ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ የነዋሪውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ የባለድርሻ አካላቱ በእውቀት፣ በእምነት፣ በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ውስጥ ራስን በማስገዛት ተባብሮ መስራት እንዳለበትም መክረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክትር አቶ ሽመልስ ታምራት አክለውም የግንባታ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዳይመራ ገፊ የሆኑ ምክንያቶችን አብራርተዋል፡፡

በባለድርሻ አካላቱ በሚፈጠር ቢሮክራሲያዊ አሰራር ፣ እንዲሁም ላለፉት ዓመታት በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ሳቢያ ሀገሪቱ የነበረችበት ነባራዊ ሁኔታ ለግንባታው ፕሮጀክት መፋጠን ጎታች መንስዔዎች እንደነበሩ የገለጹት ዋና ዳይሬክተር፣ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በከተማ አስተዳደሩ ከተዋቀረው የአብይ እና የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲሁም ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር የተሸለ የአሰራር እና የቁጥጥር ስርዓትን በመዘርጋት ተጠቃሽ ችግሮችን በተቻለ መጠን እየቀረፈ በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ቤቶችን ወደ ፑል ለማስገባት ቀን ከሌሊት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በፕሮጀክት አስራአንድ ጽህፈት ቤት በተጠራው ውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የባለቤት እድለኞች ገንቢ ሀሳቦች ፣ ሚዛናዊ አስተያየቶች፤ እና ምክንያታዊ ጥያቄዎች ከመቅረባቸውም በላይ ሰፊ የመወያያ ርእሶች ሆነው ውለዋል፡፡

ከቤት እድለኞች መሃል የተወሰኑት ውል በሚዋዋሉበት ወቅት በቅጹ ላይ የነበረው የካሬ መጠን መሬት ላይ ካለው የቤቶች ካሬ መጠን ጋር ልዩነት ያለው መሆኑ፣ የፕሮጀክት አስራ ሰባት ሳይት እና በተመሳሳይ ሌሎች ሳይቶች ላይ ተገቢውን ካሳ ሳይከፈላቸው ከሚኖሩበት እና ከሚያርሱበት መሬት ላይ ከተፈናቀሉ አርሶ አደሮች እና የአርሶአደር ቤተሰቦች ጋር ተስማምቶ ለመኖር አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸው የሚመለከተው የመንግስት አካል ክወዲሁ የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለበት አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ብሎኮች በተቀመጠላቸው “ስታንዳርድ” መሰረት አለመገንባታቸው ን የገለጹ ሲሆን በእጣ ከተላለፈላቸው ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ የገበያ ዋጋ ንረት እና የቤት ኪራይ ውድነት በኑሮዋቸው ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ተጽእኖ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በኃላፊነት እና በእኔነት ስሜት ውስጥ ሆኖ መረዳት እንደሚገባው እና በተቻለ ፍጥነት ግንባታቸው የተጠናቀቀ እና የመሰረተልማት አውታሮች የተሟላላቸው ለመኖሪያ ምቹ የሆኑ ቤቶችን ሊያስረክባቸው እንደሚገባ አቤቱታቸውን ገልጸዋል፡፡

የቤቶችልማት ኮርፖሬሽን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቶማስ ደበሌ በተቋሙ ውስጥም ሆነ በሌሎች የባለድርሻ አካላት ላይ የሚታይ የአመለካከት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ያልሰለጠነ ያሰራር ስርዓት፣ ኋላቀር የሆነ የስራ ባህላችን፣ የመሰረተ ልማት ውስንነት እና የግብዓቶች መጠን እና ጥራት ዕጥረቶችን ጨምሮ ውስብስብ የሆኑ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች ላለፉት ዓመታት ተቋሙ ለለፈባቸው ችግሮች በመግፍዔነት ሊታዩ እና ሊተኮርባቸው እንደሚገባቸው በጥልቀት እና በዝርዝር አብራርተዋል፡፡

ቢሮክራሲያዊ አመለካከቶችን በመታገል እና የነበሩ የአሰራር እና የቁጥጥር ስርዓቶችን በማዘመን የተሻለ ስራ እየተሰራ በመሆኑ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙትን “የፊኒሺንግ” ስራዎችን በተሸለ ሁኔታ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ነው የቤቶች ግንባታ ዘርፍን በበላይነት የሚመሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ቶማስ ደበሌ የገለጹት፡፡

በኮዬ ፈጬ ሳይት በ64 ኪ.ሜ እየተገነባ ያለው የመንገድ ስራን ጨምሮ የውኃ፣የፍሳሽ፣እንዲሁም የኤሌክትሪክት መሰረተ ልማት ስራዎች በተቀመጠላቸው እቅድ መሰረት እየተከናወኑ ነው ለማለት ባያስደፍርም ከባለፉት ዓመታት በተሻለ አፈጻጸም እየተሰሩ መሆናቸውን የገለጹት የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ግንባታቸው ያላለቁ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው የተጠቃሚውን ማኅበረሰብ ፍልጎት ማርካት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡