በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

ሐምሌ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

የኢትዮጵያን ሠላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መላው ህብረተሰብ ይበልጥ ተቀናጅቶ በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለበት ተጠቆመ፡፡ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች በሀገር አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ላይ እንደተጠቆመው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጶያን ሠላምና አንድነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎችን ለመመከትና የሀገሪቱን ቀጣይ የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ መላው ህብረተሰብ ከምን ጊዜውም በበለጠ ይበልጥ ተቀናጅቶ በጋራ መረባረብ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መስከረም ዘውዴ በምክክር መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ሠላምን በማረጋገጥ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል በሚደረገው ትግል ሁሉም ወገን የበኩሉን ኃላፊነት ከመወጣት በተጨማሪ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የተዛቡ ዘገባዎችን በመመከትና እወነተኛው መረጃ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ በማድረግ የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ እንዲሳካ ጠንክሮ መሥት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት በምክክር መድረኩ ላይ ባቀረቡት ሰነድ በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይ ህ.ወ.ሀ.ት በትግራይ ህዝብ ስም የሚፈፅመውን ሀገር አፍራሽ ድርጊት መላው ህብረተሰብ እንደ አንድ ሰው በመቆም መመከት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡

መንግስት የሀገር ሽማግሌዎችን ከመላክ ጀምሮ ያሉትን የሠላም አማራጮች በሙሉ መጠቀሙን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ የክረምት ወቅት ከመሆኑ ጋር በተያያተ አርሶ አደሩ የእርሻ ሥራውን በሠላም እንዲያከናውን በሚል የተወሰደውን የተናጥል የተኩስ አቁም እርምጃም ባለመቀበል በእኩይ ሥራው የቀጠለ በመሆኑ እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል ለሀገሩ አንድነት፣ ሠላምና ብልፅግና የድርሻውን መወጣት የሚጠበቅበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡

የውየይት መድረኩ ተሳታፊዎችም በዚሁ ጊዜ በሰነዘሯቸው አስተያየቶች ሀገሪቱን ለመበታተን የተነሳውን ህ.ወ.ሀ.ት የተሰኘ አሸባሪ ቡድን በጋራ መመከት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆኑን፣ በህዳሴ ግድብ እና በስደስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በጋራ በመረባረብ ስኬታማ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ሁሉ የሀገር አንድነትን ለመናድ የተነሱ ኃይሎችን ሴራ በማምከን ሠላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረትም በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ ነን መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ሠላምና አንድነት ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የሚገልፁ እና ሌሎች ነጥቦችን የያዘ ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጡ ሲሆን ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና ከተጠሪ ተቋማቱ የተውጣጡ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡