29/02/2014 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን‘’የሀገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነ አደጋን ለመከላከል በወጣው አዋጅ ቁጥር’’ 5/2014 ላይ ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ፡፡

በውይይቱ ላይ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት እና ለዚህ አዋጁ መነሻ የሆኑ ህገመንግስታዊ አንቀጾችና መሰረቶችን በተመለከተ የቢሮው የህግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብዲሳ አራርሳ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/፣ ኦነግ ሸኔ፣ የጉሙዝ ታጣቂዎች እና ሌሎችም ፀረ ሰላም ኃይሎች እኩይ ተግባር አማካኝነት እየታመሰች መሆኗ እና ሰብዓዊ መብቶችን በተለመደው የህግ ማስከበር ስርዓት ማስጠበቅ ባለመቻሉ ይህም ህገመንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ መነሻ ምክንያት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ የተፈጻሚነት ወሰኑም እንደአስፈላጊቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሊፈጸም እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

የአዋጁን አፈጻጸም በየትኛም ሁኔታ ማደናቀፍ፣ ለቡድኑ የሞራል የቁስም ሆነ ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ፣ ያለፍቃድ ስብሰባዎችን ማካሄድ፣ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመርያ እዙ አለመታዘዝ፣ ያለፍቃድ የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ እና የመሳሰሉ ጉዳዮች በአዋጁ የተከለከሉ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ አንጻር አስፈላነቱን በመግለጽ ቀደም ብሎ መውጣት እንደነበረበት በመጠቆም ለአፈጻጸሙም  የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ያስሚን ወሀብረቢ በበኩላቸው በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ ሰራተኞችን ከተዋወቁ በኋላ ቢሮው ትልቅ ሃላፊነት የተጣለበት በተቋም በመሆኑ ሁሉም ሰራተኛ በተሰማራበት የስራ መስክ ኃላፊነቱን በተገቢው መልኩ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትዋል፡፡