በመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ላይ ውይይት ተካሄደ
ጥቅምት 04/2014 ዓ.ም
በቤት ልማቱ ዘርፍ የተሻለ ስኬት በማስመዝገብ የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ ከምን ጊዜውም በበለጠ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀምን አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ባደረጉት ንግግር በተቀናጀ የቤቶች ልማት ፕሮግራም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች የመጠለያ ችግር በማቃለል ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግና የህብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ ከምንጊዜውም የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የእቅድ በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ደንቦባ በውይይቱ ላይ ባቀረቡት የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት የዕቅድ የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ በቀጣይ የተሸለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ እንዲቻል በተለይ በመሠረተ ልማት እና በፋይናንስ አቅርቦት እንዲሁም በሲሚንቶ እጥረት እና በሌሎችም ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ለውጥ ለማምጣት ጠንክሮ መሥራትና በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ላይ የውይይቱ ተሳታፊዎች በተለይ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጋር በቅንጅት የሚሠራበት ሁኔታ ቢጠናከር፣ በተለያዩ ሳይቶች በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት ክፍት ሆነው የቆዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተለይተው እንዲወጡና ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች ቢተላለፉ የሚሉና ሌሎችም የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ሰንዝረው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በዚህም መሠረት መብራትና ውሃን ከመሰሉ የመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በቅርበት መሥራት ተገቢ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በተለይም በዕቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶችን የማስፈፀም አቅም ችግርን እንዲሁም የፋይናንስ እጥረትን ለመቅረፍ የሚያስችል ስልት መቀየስና የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
በዕለቱ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነው ለተሸሙት ወ/ሪት ያስሚን ወሀብረቢ በተደረገው አቀባበል ላይ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰነዘሩት አስተያየት የቢሮው የኃላፊነት ቦታ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ደረጃ እንዲሆን መደረጉ የከተማ አስተዳደሩ ለቤቶች ልማት ፕሮግራም የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ በመሆኑ የሚያበረታታ ሆኖ እንዳገኙት አመልክተዋል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሪት ያስሚን ወሀብረቢ በበኩላቸው ከኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት በመሥራት የቤት ልማት ፕሮግራሙን ለማሳካትና የህብረተሰቡን እርካታ ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከማዕከልና ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የተውጣጡ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡